የገንዘብ ሚኒስቴር ሰራተኞች የአለም የሴቶች ቀንን አከበሩ
March 9, 2021
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የሴቶች ቀን በገንዘብ ሚኒስቴር ታስቦ ውሏል፡፡
የዘንደሮ የሴቶች ቀን የተከበረው “የሴቶችን መብት የሚያስከብር ማህበረሰብ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ያስሚን ወሀብረቢ እንዳሉት ሴቶች በሀገሪቱ እየተጫወቱ የሚገኘው ሚና እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ባለፉት ሶስት የለውጥ አመታት በሃገሪቱ ወሳኝ የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሴቶች ተሳትፎ በእጅጉ እያደገ ስለመምጣቱም አስረድተዋል፡፡
ማርች 8 የሴቶችን የትግል ታሪክ የምንዘክርበት፣ ሴቶች በታላቅ ቆራጥነት ያገኙትን ድል በማስታወስ የመጪው ዘመን ትግል በይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የምናደርግበት ዕለት ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፀዋል፡፡
ክብርት ያሰሚን በበዓሉ ላይ እንደገለፁት ይህንን ቀን የምናስታውሰው ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሀገርን ለመገንባት ለሚደረገው ትግል አጋርነታችንን በመግለጽ ነው ብለዋል፡፡
የሴቶችን መብት ማክበር፣ የሰብአዊ መብትን ማክበር ስለሆነ ለዚህ ስኬት የተደረጉ ትግሎች እንዲሁም ለሴቶች ፍትሀዊ ተጠቃሚነትና እኩልነትን ለማቀዳጀት የተከፈሉ መስዋትነቶች ሁሉ በታሪካችን ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡