የገንዘብ ሚኒስቴር በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ከዝግጅት ወደ ትግበራ ምእራፍ በስኬት በመሸጋገሩ የእውቅና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጠው
By: Yonas M. | Published: Aug. 18, 2025
ነሐሴ 12/ 2017 - የገንንዘብ ሚኒስቴር በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ከዝግጅት ወደ ትግበራ ምእራፍ በስኬት በመሸጋገሩ በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደ ስነስርአት የእውቅና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተሰጠው፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በምዕራፍ አንድ የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ማሻሻያን በ8 የፌድራል መንግስት ተቋማት ሲተገብር ቆይቶ አራቱ ተቋማት የዝግጅት ምዕራፍን በስኬት አጠናቀው ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችላቸው አቅም ላይ መድረሳቸውን ገልጽዋል፡፡
በዕውቅና ዝግጅቱ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚንስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት መንግስት ከአንድ ዓመት በፊት ተግባራዊ ያደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በወጭ ንግድ፣ በውጭ ምንዛሬ ገብይት፣ በመንግስት ገቢ እና ሌሎችም በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውንና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ዘላቂ ለማድረግ የመንግስት ሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ አስፈለጊ በመሆኑ በመኩራ ደረጃ ከተመረጡ መስሪያ ቤቶች መካከል ገንዘብ ሚንስቴር አንዱ የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ ዝግጅቱን በስኬት አጠናቆ ወደ ትግበራ ምእራፍ መሸጋገሩን አመልክተዋል፡፡
ሚንስትሩ በቀጣይ ማሻሻያውን ሙሉ በመሉ ወደ ተግባር ለማዋል ሰራተኛውን በመመዘን በአዲስ አወቃቀር የስራ ምደባ እንደሚደረግና ሰራተኛው ራሱን ለዚህ ማዘጋጀት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ዕውቅናውን ለገንዘብ ሚኒስቴር ያበረከቱት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነሩ ዶ/ር መኩሪያ ሀይሌ በበኩላቸው ሁለት ብስራቶችን ይዘው እንደመጡ ተናግረው፤ የመጀመሪያው የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ማሻሻያን የዝግጅት ምእራፍ በመጀመሪያ ዙር ከተመረጡ 8 ተቋማት በስኬት በማጠናቀቅ ወደ ተሟላ ትግበራ መሸጋገሩንና
ሁለተኛው ደግሞ ለመንግሰት ሰራተኞች ከመስከረም 2018 ጀምሮ የደመወዝ መሻሻያ መደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር መኩሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ማሻሻያን በዝግጅት ምዕራፍም ወቅት ያሳየውን ስኬት በትግበራውም ምእራፍ በመድገም ለሌሎች የፌድራልና የክልል ተቋማት አርአያ መሆን ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡
የደመወዝ መሻሻያውን አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የደመወዝ ማሻሻያውን ለማድረግ መንግስት ባለፋት ወራት በቂ ዝግጅት ሲያርግ መቆየቱንና ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ የጭማሪው ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡
መንግስት ባለፈው ዓመትም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ሲያደርግ በተለይ ዝቅተኛ ደመወዝ ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ከፍ ያለ ጭማሪ ማድረጉን፣ ነዳጅና ማዳበሪያን በመደጎም የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውሰው፤ አሁን የመንግስት ሰራተኛውን ደመወዝ ለማሻሻል 160 ቢለየን ብር በጀት መያዙንና በቀጣይ የመንግስት ገቢን ለማሳደግ፣ ወጪን በመቀነስና የውጭ ሀብት በማሳብሰብ በኩል ተግተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡