የገንዘብ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የገንዘብ ቢሮዎች የጋራ የምክክር መድረክ ተጀመረ
Published: April 1, 2026
መጋቢት 23 2018 የገንዘብ ሚኒስቴር እና የሁሉም ክልሎች የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የሁለት ቀን የምክክር መድረክ ተጀምሯል። በመድረኩ ላይ እየተተገበረ ባለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤቶች፣የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ፣ በዲጂታል የክፍያ ስርዓት ዝርጋታ እና በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ ሰፊ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
የምክክር መድርኩን በንግግር የከፍቱት የገንዘብ ሚኒስቴር የፊስካል ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፍቃዱ ሆረታ እንደተናገሩት የጋራ የምክክር መድረክ ዋነኛ ዓላማ እየተተገበረ ባለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ፣ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እና ዲጂታል ሲስተም ከመዘርጋት አንጻር የተገኙ ውጤቶች፣ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ላይ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ መውሰድና የወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብልዋል።
በፌዴራል መንግሥት የመንግሥት ግዢ ሥርዓትን በማዘመን ቀልጣፋ፣ ግልጽና ፍትሃዊና አድልዎ የሌለበት እንዲሁም ለግዢ የሚውለውን ከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብ በተሻለ ሁኔታ ቁጠባና ውጤታማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል ሲሉ ሚንስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ዘመናዊ የመንግሥት ፋይናንስ አሠራር ከመዘርጋት አንፃር የፌዴራል በጀት መሥሪያ ቤቶች ክፍያቸውን ቀጥታ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት እንዲፈጽሙ ማድረግ፣ የፌዴራል የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን በአብዛኛው በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ላይ እየተተገበረ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የፕሮግራም በጀት በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እየተተገበረ ሲሆን የመንግሥት ዘርፍ የሂሳብ አያያዝ እና አቀራረብ ደረጃዎች (IPSAS) ለመተግበር በመንግሥት ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ የስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የምክክር መድርክ ላይ የመንግስት ፋይናንስ ማሻሻያ፣የነጠላ ትሬዥሪ እና የኤልክትሮኒክ ክፍያ ስራዓቶች ፣ በመንግስት ፋይናንስ አስተዳድርና የበጀት አሰተዳደር፣ የገንዘብ ሴክተር የመንግስት አግልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ርዕስ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል።