የገንዘብ ሚኒስቴር ከተለያዩ አልሚዎች ጋር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመ

By Yonas | Published: July 3, 2025

ሰኔ 26 2017 . - የገንዘብ ሚኒስቴር በመንግሥት እና የግል አጋርነት ማእቀፍ ከተለያዩ አልሚዎች ጋር የፕሮጀክት ስምምነት በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈራረመ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ በፊርማው ስነስርአት ላይ አንደገለጹት የመንግስትና የግል አጋርነት ተግባረዊ ለማድረግ የሚያስችል ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ መዘርጋቱን ጠቅሰው በዛሬው እለት የተፈረሙት ስምምነቶች ሙሉ በሙሉ ተግባረዊ ሲደረጉ በአገራችን ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ላይ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

በእለቱ የሰባት ፕሮጀክቶች ስምምነት የተፈረመ ሲሆን ፕሮጀክቶቹም፡-

  1. ከፊል የጫካ የቤት ልማት ፕሮጀክት ሎት A1 ፕሎት 4 እና 7 አጠቃላይ ስፋቱ 5.7 ሄክታር የሆነ በድምሩ 1,200 መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ G+6 የገበያ ማዕከል የያዘና ጠቅላላ ወጪው 32.37 ቢሊዮን ብር የሚወስድ ICE Home Development and Construction PLC ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚከናወን፣
  2. ከፊል የጫካ የቤት ልማት ፕሮጀክት ሎት A1 ፕሎት 12 አጠቃላይ ስፋቱ 9.452714 ሄክታር የሆነ በድምሩ 1,852 መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሁለት (2) የገበያ ማዕከል የያዘና ጠቅላላ ወጪው 23.06 ቢሊዮን ብር የሚወስድ OVID Chaka Housing Development PLC ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚከናወን፣
  3. ከፊል የጫካ የቤት ልማት ፕሮጀክት አጠቃላይ ስፋቱ 9.45 ሄክታር የሆነ በድምሩ 1,123 መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ 48 ሱቆችን የያዘና ጠቅላላ ወጪው 11.7 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከግል ባለሃብት ጋር ጥምረት በመፍጠር በየካ ክፍለ ከተማ የሚከናወን፣
  4. የጥይት ቤት የቤት ልማት ፕሮጀክት አጠቃላይ ስፋቱ 4.5038 ሄክታር የሆነ በድምሩ 1,823 መኖሪያ ቤቶችን እና የገበያ ማዕከል የያዘና ጠቅላላ ወጪው 4.31 ቢሊዮን ብር የሚወስድ OVID Kings Tower PLC አራዳ ክፍለ ከተማ የሚከናወን፣
  5. የአዋሽ ፏፏቴ ሪዞት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት አጠቃላይ ስፋቱ 11.6 ሄክታር የሆነ 50 ቅንጡ የማደሪያ ክፍሎችና ሌሎች መሰረተ-ልማቶች የተሟሉለትና ጠቅላላ ወጪው 813.51 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ Boston Partners PLC በአዋሽ ፓርክ ውስጥ የሚከናወን፣
  6. የደንቢ ሐይቅ ሎጅ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት አጠቃላይ ስፋቱ 36.67 ሄክታር የሆነ፣ 15 ቡንጋሎዎ፣ ሪስቶራንትና ሌሎች መሰረተ-ልማቶች የተሟሉለት ጠቅላላ ወጪው 125.89 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ እና MIDROC Investment Group በበበቃ የሚከናወን፣
  7. የተቀናጀ የዲያግኖስቲክ አገልግሎት ማዕከል፡- ፕሮጀክቱ የላብራቶሪ፣ የኢሜጂንግና የፓቶሎጂ አገልግሎቶችን በጥራት ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ስድስት ሆስፒታሎች እንዲቀናጁ የተደረገ ሲሆን ተግባራዊ የሚደረገውም በቅዱስ ጴጥሮስ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሆኖ አጠቃላይ ወጪውም 5.2 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ Ceraba Lancet Africa(CLA), International Clinical Laboratories (ICL) እና Pioneer Diagnostic Center (PDC) በሚያቋቁሙት የፕሮጀክት ኩባንያ መሰረት ተግባራዊ ይደረጋል

መንግሥት የመንግሥት እና የግል አጋርነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ዘርግቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አድርጓል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ መንግሥት ማቅረብ የነበረበትን የመሠረተ-ልማትና የሕዝብ አገልግሎት ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ በዘርፉ የተሰማሩና ልምድ ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሃብቶች፣ የውጭ ባለሃብቶች እንዲሁም የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጥምረት (Consortium) መስርተው መሠረተ-ልማትና የሕዝብ አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት፣ በጤና፣ በቤቶች፣ በሎጅስቲክስ እና በቱሪዝም ዘርፎች ለመንግሥት እና ለግል አጋርነት ተስማሚ የሆኑ 34 ፕሮጀክቶች ተለይተው በተለያዩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቶች የሚጠበቅባቸውን ሂደት አልፈው አሸናፊው ኩባንያ ሲለይ፤ የመግአ ስምምነት በመፈጸምና ኩባንያዎቹ ፕሮጀክቱን ለማበልጸግ የሚያስችለውን ፋይናንስ በብድር እና ከኩባንያው መዋጮ (Equity) በማሰባሰብ ወደ ሥራ እንዲገባ ያደርጋል፡፡

መንግሥት .. ኦገስት 17, 2024 620 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የአይሻ-1 300 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም ያለውን የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በመግአ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን የኃይል ግዢ እና የትግበራ ስምምነት AMEA POWER AYSHA WIND ONE PLC ጋር ፈጽሟል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የመግአ መምሪያም በመግአ የፕሮጀክት ዝርዝር ውስጥ ያሉትን እና በቀጣይ በፕሮጀክት ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱትን ፕሮጀክት አስፈላጊውን ቅድመ-ሁኔታዎች እንዲያሟሉ በማድረግ ወደ ተግባር የማሸጋገር ስራውን ከባለድርሻ አካለት ጋር ሆኖ በቅንጅት እንደሚሰራ ታውቋል፡፡

 

192 Views