የገንዘብ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ ባለስልጣናት ጋር ፍሪያማ ውይይት አካሄደ
Dec. 8, 2023
ሕዳር 28 / 2016 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢጀርድና ከአለም ባንክ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ ጋር በሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚና ልማት ጉዳይ ላይ በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፍሪያማ ውይይት አካሄደ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በውይይቱ ወቅት የአለም ባንክ የኢትጵያ ትልቁና ዘላቂ የልማት አጋር መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ባላት የህዝብ ብዛትና የተፈጥሮ ሀብት በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት በመሆኑ የልማት አጋሮች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት በክፍለ አህጉር ደረጃ እንዳደረጉት ኢንቨስትመንት ይቆጠራል ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከአለም ባንክ ጋር ያላት የልማት ትብብር ውጤታማ መሆኑንና እስካሁን በኢትጵያ በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በጥሩ አፈጻጸም ላይ የሚገኙ መሆኑን አመልክተው በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ሪፎርምን ውጤታማነት ለማረጋገጥ፣ የግል ዘርፉን ለማጎልበት፣ የመልሶ ማቋቋምን ተግባራዊ ለማድረግ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማጠናከር፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጎልበትና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን ለማፋጠን ከአለም ባንክ ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚጠበቅ አስረድታዋል፡፡
የአለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢጀርድ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚና ልማት ላይ በተለያዩ ጊዚያትና ስፍራዎች ከአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በመሆን ከኢትጵያ ባለስልጣናት ጋር ፍሪያማ ውይይት መካሄዱን ጠቁመው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማድረግ፣ የግል ዘርፉን ለማጠናከር፣ የመሰረተ ልማት ለማስፋፋት፣ የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን ለማጠናከርን የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት የአለም ባንክ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ የብሄራዊ ባንክ ገዢ ክቡር አቶ ማሞ ምህረቱ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው እነዲሁም ሌሎች የገንዘብ ሚኒስቴርና የአለም ባንክ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡