የገንዘብ ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን ሚንስትሩ ገለጹ
April 9, 2025
ሚያዚያ 1 /2017 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን ሚንስትሩ ክቡር አቶ አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የ8 ወራት የስራ አፈጻጸም ለመገምግምና የከተማ የመስክ ምልከታ ለማድግ ዛሬ በተቋሙ በተገኘበት ወቅት ክቡር ሚኒስትሩ እንደገለጹት የፊሲካል ፖሊሲውን በአግባቡ ተግባራዊ በማድግ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት፣ ታክስ ፖሊሲን ተግባረዊ በማድረግ፣ ለመሰረታዊ ግብአቶች ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ፣ የበጀት ጉድልትን በአግባቡ በማስተዳደር፣ የእዳ ሽግሽግና እፎይታ እንዲገኝ በማድረግ፣ የውጪ ሀብትን ከምንጊዜውም በላይ በማሰባሰብና የሀገር ወስጥ ገቢን በማሳደግ በአጠቃላይ የመንግስትን ፋይናንስ በአግባቡ በማስተዳደር የማሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ፕሮግራም ውጤታማ በማድረግ ተቋሙ ሀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የፊሲካል ፖሊሲንና የመንግስት ፋይናንስን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ባለፉት 8 ወራት ተቋሙ የኑሮ ወድነት የሚያድግበትን ፍጥነት ከመቀነስ፣ በተለያዩ የታክስ ፖሊሲ ህጎች ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከማገዝ፣ ከጥሬ ገንዘብ አስተዳደር አንጻር ክፍያዎች በተለይ ለክልሎች በወቅቱ እንዲለቀቅ በማድግና የኦዲት ግኝቶች ላይ ተገቢውን እርምጃ ከመውሰድ አንጻር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው በሚቀጥለው የ2018 በጀት አመትም የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ፕሮግራሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የዋጋ ንረቱ ሚጨምርበት ፍትነት ይበልጥ እነዲቀንስ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ በሰጡት አስተያት በተቋሙ ምድረ ጊቢና በስራ ክፍሎቹ ተዘዋውረው ባዩት ምቹ የስራ ሁኔታ በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ከመንግስት ፋይናስ አስተዳደር አንጻር የአንዳንድ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ የመንግስት ንብረት አስተዳደርን፣ የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዢ፣ በክልሎች የፕሮጀክት አፈጻጸም የጥሬ ገንዘብ ፍሰት፣ በኦዲት ግኝት እርምጃ አወሳሰድና በሌሎች የፊሲካል ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሻሻል ስላለበቸው ጉዳዮች ግብረ መልስ ሰጥተዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተቋሙ የ8 ወራት የስራ አፈጻጸም ላይ ላነሱት ጥያቆዎች ክቡር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴና ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡