የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለፈረንሳይ ኩባንያዎች ማብራሪያ ሰጡ
March 9, 2021
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለፈረንሣይ ኩባንያዎች ለማስተዋወቅ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ፈረንሳይ ውስጥ ከሚገኘው ትልቁ የአሠሪዎችና ኩባንያዎች ማህበር ኤም.ኢ.ዲ.ኢ.ኤፍ ኢንተርናሽናል ተሳትፎ አድርጓል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ውይይቱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ መንግስት በማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ስላደረገው ጥረት እና የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ቁልፍ ሚና ለማሳደግ እየተወሰዱ ስላሉ የፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያዎች ለፈረንሳይ ኩባንያዎች አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑንም ጠቅሰው፣ በአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳደግ እና ብዘሀነት በማስፋት ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ኢዮብ በኢትዮጵያ ከሐምሌ እስከ ታህሳስ 2013 ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንደተመዘገበ አብራርተዋል፡፡ ሀገሪቱ ትኩረት የምትሰጣቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች አግሮ ፕሮሰሲንግ ፣ ቱሪዝም ፣ ማኑፋክቸሪንግ ፣ ማዕድንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ መሠረት የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እ.ኤ.አ ከ1996 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ4.7 ቢሊየን ብር በላይ ያፈሰሱ ሲሆን፣ ከ4000 በላይ ቋሚ እና ከ2700 በላይ ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ ኩባንያዎቹ የተሰማሩት በማኑፋክቸሪንግ ፣ በግብርና ፣ በሪል እስቴት ፣ በሆቴሎች ፣ በቱር ኦፕሬሽንና በሌሎችም መስኮች ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በ19 ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ጀምሮ ረጅምና ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት ያለቸው መሆኑን ይታወቃል
ስብሰባው የተካሄደው በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው፡፡