የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ

Jan. 17, 2023

ጥር 9 / 2015 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው  በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶ/ር አኔት ዌበር ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካካል ስለሚኖረው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትብብር በጽ/ቤታቸው ተወያዩ፡፡

ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በውይይቱ ወቅት የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት አጋር መሆኑን ጠቅሰው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትና ሁለተኛውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማፋጠን እየተደረጉ ሰላሉ ጥረቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በግጭት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን  በዘላቂነት  ለማቋቋምና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ሀብት ማሰባሰብ ስለሚያስፈልግ ሀገሪቱ እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ ዘላቂ የልማት ሀጋሮች በዚህ ረገድ የሚያበረክቱትን የሰብአዊ እርዳታና የልማት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶ/ር አኔት ዌበር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን ለማረጋጋትና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያላት ሀገር በመሆኗ በኢትጵያ ሰላም መስፈኑ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጠናከር በጣም አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ከኢትጵያ ጋር ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ወደ ነበረበት ለመመለስና ብሎም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቀጣይነትም ተከታታይ ውይይት በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ላማድረግ በህብረቱ በኩል ቁርጠኝነት እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡

537 Views