የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በ115ኛው የአፍሪካ ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ጉባኤ የኢትዮጵያን አቋም ገለጹ
Nov. 28, 2022
ህዳር 19 / 2015 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በቤልጂየም ብራስልስ እየተካሄደ ባለው 115ኛው የአፍሪካ ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር የኢትዮጵያን አቋም አንጸባርቀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ የኢትዮጵያን የልኡካን ቡድንን በመምራት በጉባኤው ባሰሙት ንግግር የአፍሪካ ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት ተልእኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ማሻሻያዎችን በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ አለበት ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
ከአለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ አንጻርም በቅርቡ በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ በተካሄደው አለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የተነሱት ቁልፍ ጉዳዮችና ውሳኔዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገቡም አስረድተዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ አያይዘውም የአፍሪካ ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት አባል ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ለሆኑ አገራት የጉዳት ካሳ ለመስጠት የተመሰረተው ፈንድ በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ ታዳጊ ሀገራት ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ድምጻቸውን ማሰማት አንደሚገባቸውም አመልክተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ የኢትዮጵያን ልኡካን ቡድን መርትው በጉባኤው ከመሳተፍ በተጓዳኝ በስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ከአፍሪካ ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ ሀገራት ድርጅት አባል ሀገራት እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት አባላት ጋር የሁለትዮሽ ውይይትና የልማት አጋርነት ውይይቶችን እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡