የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማዘመንና የበለጠ ውጤታማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ጉብኘት ተደረገ

March 3, 2022

በገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ በክብርት ወ/ሮ ሰመሬታ ሰዋሰው የተመራ ልዑክ በኦሮሚያ እና በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ስር የሚገኙት የቡልቡላ እና የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ የልዑካን ቡድኑ የቡልቡላ እና የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሥራ እንቅስቃሴ የተመለከተ ሲሆን የፓርኮቹ ስራ አስኪያጆች እና በክልሎቹ የኢንዱስትሪ ፓርክ ቢሮ ሃላፊዎች በኩል ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሬታ ሰዋሰው ስለተደረገላቸው አቀባበልና ማብራሪያ ያመሰገኑ ሲሆን በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የግብርናው እና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማዘመን እና ለማስተሳሰር በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን በማስታወስ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን የበለጠ ውጤታማ በማድረግ ረገድ የሚያበረክቱትን አስተፅኦ ማሳደግ እንዲችሉ ቀጣይ ድጋፎች እንደሚደረጉም ገልጸዋል፡፡

የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በተለይም በአጎራባች ከሚገኙ ክልሎች ጋርም የኢኮኖሚያዊ ትስሰር ለመፍጠር እንደሚያስችልም አብራርተዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መሉ በመሉ ወደ ስራ ሲገቡ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፈጠሩም በላይ የሀገራችን አርሶ አደሮች ከተሻለ የአመራረት ዘዴዎች ጋር እንዲተዋወቁና እና ያመረቱትንም ምርት ለገበያ በማቅረብ ምርቱን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ ይረዳል ብለዋል፡፡

መንግስት የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ለሚገነቡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች የተለያዩ ድጋፎች እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡በሌላ በኩል በፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅርፍ ትኩረት ተሰጥቶበት በቀጣይነት እንደሚሰራም ሚኒሰቴር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ ኦሬሊያ ፓትሪዛ እንደተናገሩት ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ከመተካት ባሻገር በጥራት ተወዳዳሪ ምርቶችን በማቅረብ በምሰራቅ አፍሪካ ያለውን የገበያ ዕድል ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጎበኙበት ወቅት የገንዘብ፣የግብርና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የኢንዱሰትሪ ልማት ድርጅት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጉበኝቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

702 Views