የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎችና የኤሌክትሮኒክስ አጠቃቀምና አወጋገድ መሻሻያ ላይ ትኩረት ያደረገ ዕወደ ጥናት ተካሄደ

March 9, 2021

በግብርና፣ኢንዱስትሪ ኬሚካሎችና በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አያያዝ፣ አጠቃቀምና አቀማመጥ በርካታ ችግሮች እንደሚታዩ የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ ተገለፀ፡፡

በዐውደ ጥናቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ያስሚን ወሀብራቢ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ አዲሱ የአስር አመት የልማት ዕቅድ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ምጣኔ ሀብትን ለመገንባት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

በልማት ዕቅዱ ላይ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የዱር እንስሳትና ሌሎች የብዝሀ-ህይወት ደህነትና ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ስራው ዘለቄታዊነት እንዲኖረው በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ያሉ በካይና ምርዛማ የግብርና ኬሚካሎች፣ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎችና የኤሌክትሮኒክስ ተረፈ ምርቶች በሳይንሳዊ መንገድ መወገድ አለባቸው ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር መስፍን ረዲ እንዳሉት በኢትዮጵያ የግብርና ኬሚካሎች መጠቀም እያደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ኬሚካሎች በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡ አንዳንዴም በአሰራር ጉድለት የተነሳ አረምና የሰብል ተባዮችን ለመከላከል ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የኬሚካል ምርቶች ጥቅም ላይ ሳይውሉ ዘመን እንደሚያልፍባቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር 2607 ቶን ልዩ ልዩ የግብርና ኬሚካል በትብብር መወገዱን ገልፀዋል፡፡

ምርትን ለማሳደግ የምንጠቀምበት የግብርና ኬሚካል ከአያያዝና አጠቃቀም ጉድለት የተነሳ የጤና ጉዳት እንዳስከትል በቀጣይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የግብርና እና የኬሚካል ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ ብሎም የሰው ሀይል አስተዳደርን ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስራዎች እንደሚሰሩ በአውደ ጥናቱ ተገልፆዋል፡፡

929 Views