የጤናውን ዘርፍ በበጀት ለመደገፍ እንዲቻል ተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ ጥናት እንዲደረግ አቅጣጫ ተሰጠ፡፡

May 10, 2022

ግንቦት 2 / 2014 ዓ.ም - የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ መስሪያ ቤቶች የ2015 አመት የበጀት እቅዳቸውን ለገንዘብ ሚኒስቴር ሲያቀርቡ  የጤናውን ዘርፍ በበጀት ለመደገፍና ለማጠናከር እንዲቻል አቅም ያላቸው ታካሚዎች ከአገልግሎቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጠ፡፡

የበጀት ስሚ መርሀ ግብሩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ እንደገለጹት መንግስት የጤናወን ዘርፍ በበጀት ለመደገፍ አቅም በፈቀደ መጠን ጥረት እንደሚያደርግ አመልክተው የጤና ተቋማት ለሚሰጡት አገልግሎት በጣም ዝቅተኛ ክፍያ ነው የምንቀበለው የሚለውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ  አቅም ያለውንና የሌለውን በመለየት አቅም ያላቸው ታካሚዎች ከአገልግሎቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነና ተገቢ  ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ እንዲቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

የጤና መድህን ዋስትና ለዘላቂ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ስትርቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዶ/ር እዮብ ጠቁመው የጤና ተቋማት አገልግሎት በመስጠት የሚያገኙትን የውስጥ ገቢ የሀገሪቱ የፋይናነስ አስተዳደር ደንብ በሚፈቅደው መሰረት በአግባቡና ከሙስና በጸዳ መልኩ ጥቅም ላይ የሚያውሉበት ስልት እንዲነደፍም አመላክተዋል፡፡

የ2015 አመት የበጀት እቅዳቸውን በገንዘብ ሚኒስቴር ያስገመገሙት የጤና ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙት 11 ተጠሪ ተቋማት ለመጪው በጀት አመት ያቀረቡት የበጀት እቅድ ገንዘብ ሚኒስቴር ካስቀመጠው የበጀት ጣሪያ በላይ በመሆኑ ውስን የሆነውን የገር ሀብት በቁጠባና በአግባቡ መጠቀም ይቻል ዘንድ ጤና ሚኒሰቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት የበጀት እቅዳቸውን አስተካከለው እንዲያቀርቡ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ 

1104 Views