የፌደራል መንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2015 በጀት አመት የበጀት ሰሚ ተጀመረ
May 4, 2022
ሚያዚያ 26 / 2014 ዓ.ም ፡- ገንዘብ ሚኒሰቴር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመንግስትን በጀት ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውልና ፍሪያማ የፋይናንስ አሰተዳር ስርዓት እንዲሰፍን የወጪ ቅነሳ ተግባራዊ እንዲያደረጉ አሳሰበ፡፡
ለሁለተኛ ቀን የዘለቀው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2015 አመት በጀት ሲገመገም የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ እነዳሳሰቡት የወጪ ቅነሳ ጉዳይ የ2015 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው በበጀት አመቱ አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳማይኖሩና ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው ንብረት ተውቆ በአንድ የመረጃ ቋጥ ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ የገንዘብ ሚኒሰቴር ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በቀጣይ የክትትልና የቁጥጥር ስርአት እንደሚዘረጉ አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒሰቴር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝም በበኩላቸው እንደገለጹት ገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ የፕሮግራም በጀት ክትትልና ግምገማ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የካፒታል ፕሮጅክቶች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሰተካከል የተለያዩ ስራዎችን ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውና የፋይናንስ ስርአቱን በህጉ መሰረት ተግባራዊ ባላደረጉ የተቋማት ኃላፊዎችና ባለሞያዎች ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ጨምረው አመልክተዋል፡፡
በበጀት ስሚ ፕሮግራሙ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ከተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ በላይ ያቀረቡ ሲሆን በምክንያትነት ካቀረቡት ጉዳዮች ውስጥ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ፣ የምግብ፣ የሌሎች ሸቀጦችና የመድሐኒት ዋጋ መጨመር እንዲሁም ያልተጠናቀቁ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ስራ መኖራቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የተማሪዎች የምግብ አቅርቦትና ሌሎች የምግብ ሸቀጦች በአግባቡ መተመን ይቻል ዘነድ ዝርዝር ጥናት በባለሞያዎች ተጠንቶ ለውሳኔ ለበላይ አካል እንዲቀርብ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጤታማ የስራ አፈጻጸም እውን እንዲሆን የክትትልና የቁጥጥር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡