የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ስሚ ተጀመረ
April 24, 2023
ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም - በየዓመቱ የበጀት የጊዜ ዑደቱን ጠብቆ የሚደረገው የበጀት ስሚ ፕሮግራም የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማትን የ2016 በጀት በመስማት ተጀመረ፡፡
የበጀት ስሚ ፕሮግራሙን በሚኒስቴሩ መሰብሰቢያ አዳራሽ ያስጀመሩት የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የመደበኛና የካፒታል በጀታቸውን በተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት ማቅረብ አንዳለባቸው አመልክተው የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚመደብላቸውን በጀት በአግባቡና በቁጠባ የመጠቀም አላፊነት አንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የ2016 በጀቱን ያቀረበው የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በውጭ ሀገራት ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቀሰው በሀገር ውስጥም ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያደርገውንም ጥረት የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበለጠ ውጤት የሚያስመዘግቡበትን ስልት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው በ2016 በጀት ዓመት ተቋማቱ በሂደት ላይ ያሉ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር በተጨማሪም የባህልና ስፖርት፣ የገቢዎች ሚኒስትርና ተጠሪ ተቋማት የ2016 በጀት ዝግጅታቸውን አቅርበዋል፡፡