ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ወታደር ነው !

Aug. 24, 2021

ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ወታደር ነው ሲባል ሁሉም ሰው የጦር መሳሪያ ታጥቆ ጦር ሜዳ ይሰለፋል ማለት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የስራ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ተግባርና ሀላፊነት ከተወጣ የሀገሩን ህልውና ከሚያስጠብቀው ወታደር ባልተናነሰ መልኩ ለሀገሩ ዘብ ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራርና ሰራተኞችም ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ በተጋረጠባት በዚህ ፈታኝ ወቅት ተግባርና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ከተወጡ የሀገሩን ህልውና ለማስጠበቅ ከሚዋደቀው አንድ ወታደር ባልተናነሰ ለሀገራቸው ህልውና አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይቆጠራል፡፡

በዚህ የኢኮኖሚ አሻጥር በተንሰራፋበትና የኑሮ ውድነት ዜጎችን ክፉኛ ባማረረበት ወቅት የመንግስትን በጀትና ንብረት ከብክነትና ሙስና በመጠበቅ ለታለመለት አላማ በአግባቡና በቁጠባ እንዲውል ማድረግ በጦር ሜዳ ከሚደረገው ተጋድሎ አይተናነስም፡፡

ለመደበኛ ወጪ፣ ለካፒታል ወጪ፣ ለክልሎች ድጎማና ለዘላቂ የልማት ግቦች እንዲውል የታቀደውን የ2014 በጀት አመት 561.7 ቢሊዮን ብር በጀት እንዲሁም የመንግስት ሀብትና ንብረት ከሙስና በጸዳ፣ በቁጠባና በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ማስቻል በዚህ ፈታኝ ወቅት ከእያንዳንዱ የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሰራተኛ ይጠበቃል፡፡ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ወታደር ነው ማለት ትርጉሙ ይኧው ነው፡፡

የሐገር ህልውና የሚረጋገጠው በጦር ሜዳ ከጠላቱ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ በሚዋደቀው ወታደር ብቻ ሳይሆን ተግባርና ሀላፊነቱን በአግባቡ በሚወጣ ደጀን ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎም ጭምር ነው፡፡

3064 Views