ኢትዮጵያና ቻይና የ1.22 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ተፈራራሙ
Feb. 14, 2023
የካቲት 7/2015 ዓ.ም - ኢትዮጵያና ቻይና ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት መለዋወጫ የሚውል የ1.22 ቢሊዮን ብር (የ155 ሚሊዮን የቻይና ዩዋን) የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈራራሙ፡፡
በፋይናንስ ድጋፉ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት 5 ሲስተሞች የሚውሉ 573 ዓይነት የመለዋወጫ እቃዎች የሚሟሉ ሲሆን ይህም የመለዋወጫ ድጋፍ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ተመልክቷል፡፡
ይህ የድጋፍ ስምምነት በቻይና እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ከሁለት ዓመት በፊት በተፈረመው የኢኮኖሚ እና የቴክኒክ ትብብር ስምምነት መሰረት የተከናወነ መሆኑም ታውቋል፡፡
ስምምነቱን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የገንዘብ ሚንስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ እና የቻይናን መንግስት በመወከል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛሆ ዚዩሀን ፈርመውታል፡፡