ከልማት አጋሮች ጋር በዘጠኝ ወር የኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተደረገ

May 20, 2022

ግንቦት 12/2014 አዲስ አበባ - የገንዘብ ሚኒስቴር ከልማት አጋር ሀገሮች አምባሳደሮችና የልማት ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች ጋር በሀገሪቱ የዘጠኝ ወር የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ ዛሬ ውይይት አድርጓል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የዘጠኝ ወር የማክሮ ኢኮኖሚውን አፈፃፀም ሪፖርት የፕላንና ልማት ሚንስትሯ ዶ/ር ፍፅም አሰፋ ሲያቀርቡ እንዳሉት ባላፋት ዘጠኝ ወራት ኢኮኖሚው በየዘርፋ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በውጭ ቀጥተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ወደ ሀገር ውስጥ በሚልኩት ዶላር ረገድ ጥሩ ዕድገት አለ ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በዘጠኝ ወር ውስጥ ኢኮኖሚው 6 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል ያሉት ዶ/ር ፍፁም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለ 1 ነጥብ 4 ሚለዮን ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረ፣ የመንግስት ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት እንደሳየ፤ እንዲሁም ባንኮች 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር ቁጠባ መሰብሰብ እንደቻሉ፣ በአጠቃላይ ከተሰራጨው ብድር ውስጥም 70 በመቶው ለግሉ ዘርፍ አገልግሎት ላይ እንደዋለ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት ኢኮኖሚው በወጪ ንግድ፣ በውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ፍሰትና በሌሎችም መመዘኛዎች ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ ተናግረው ነገር ግን ኢኮኖሚው በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት፣ ድርቅ፣ ኮቪድ 19 እና በሩስያ ዩክሬን ግጭት ምክንያት እየተፈተነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

መንግስት በተለይ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት ሚንስትሩ የሰሜኑን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትም ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግስት ኢኮኖሚው የገጠመውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ እንደ ድርቅ ፣ በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን ለማገገም፣ እንዲሁም መሰረታዊ የመገልገያ ሸቀጦችና መሰል ጉዳዮችን በመለየት እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም መንግስት የሀገሪቱን ዜጎች በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደርገው ጥረት ከልማት አጋሮች አላማ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ግንኙነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ልንሰራ ይገባል ሲሉ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል፡፡

630 Views