የብሔራዊ የምክክር ሂደቱን በፋይናንስ ለመደገፍ የሚያስችል የፕሮግራም ሰነድ ተፈረመ

Sept. 28, 2022

መስከረም 18 / 2015 ዓ.ም - የብሔራዊ የምክክር ሂደቱን በፋይናንስ ለመደገፍ የሚያስችል የፕሮግራም ሰነድ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም መካከል ተፈረመ፡፡

ለሶስት ዓመት ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ የፕሮግራም ሰነድ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ከልማት አጋሮች ፈንድ ለማሰባሰብ የፋይናንስ ቋት በመክፈት የሚያስተዳድር ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በበኩሉ እንደ አንድ የልማት አጋር የብሔራዊ የምክክር ሒደቱን በፋይናንስ ለመደገፍ 2.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መመደቡ ታውቋል፡፡

የተባባሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በሚከፍተው የፋይናንስ ቋት በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ከልማት አጋሮች 32.8 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ገንዘብ ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡

መንግስት ለብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሚመድበው አመታዊ በጀት በተጨማሪ ይህ በተባባሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በሚከፈተው የፋይናንስ ቋት ከልማት አጋሮች የሚሰበሰበው ፋይናንስ ነጻ በሆነ የባለአደራ ፈንድ (ትረስት ፈንድ) እንደሚተዳዳርም ተገልፆል፡፡

የትረስት ፈንዱ መቋቋም የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ተልእኮውን እንዲወጣ ማለትም ኮሚሽኑ በአዋጁ የተሰጡትን ኃላፊነቶች እንዲውጣ ተቋማዊ አቅሙን ለማጎልበት፣ሁሉን አካታች እና አሳታፊ ሀገራዊ ምክክሮችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማስጀመር እንዲሁም በሀገሪቱ ወሳኝ የልዩነት ምክንያቶች ዙሪያ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ምክረ-ሐሳቦችን ለማመንጨት በሚያደርገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡  

በመሆኑም ዛሬ የፕሮግራም ሰነዱ በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም መካከል በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈርሟል፡፡  

 

1102 Views