የገንዘብ ሚኒስትሩ በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ከተለያዩ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

Jan. 25, 2023

ጥር 17 / 2015 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች ጋር በሚኒስቴሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ወቅት በመልሶ ማቋቋም ሴክሬቴሪያትና በባለድረሻ አካላት የተጠናውና በግጭት አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት መጠን በየዘርፉ የቀረበ ሲሆን በሚቀጥሉት አምስት አመታት የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ ዝርዝር አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የመልሶ ማቋቋሙ ፕሮጀክት ዝርዝር አፈጻጸም በቅርቡ ለህዝቡና ለባለድረሻ አካላት ይፋ አንደሚደረግ ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸው በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ የላቀ ድርሻ ያላቸውትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የውሀና ኢነርጂ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይና በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በርካታ ስራ ስለሚጠብቃቸው የፕሮጀክት አፈጻጸም አቅማቸውን እንዲያጠነክሩ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የውሀና ኢነርጂ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይና ሌሎች ሚኒስትሮች ከየዘርፋቸው አንጻር በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ መካተት አለባቸው ያሏቸውን ሀሳቦች በግብአትነት ያቀረቡ ሲሆን የሴቶችና የህጻናት ጉዳይም ትኩረት አንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡    

 

207 Views