የገንዘብ ሚኒስትሩ ከዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

Jan. 23, 2023

ጥር 15 / 2015 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ከዴንማርክ የልማት ትብብርና አለም አቀፍ የአየር ንብረት ሚኒስትር ከሚስተር ዳን ጀርገንስ ጋር በሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብርና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጽ/ቤታቸው ተወያዩ፡፡

በውይይታቸው ወቅት ክቡር ሚኒስትሩ ከሰላም ስምምቱ በኋላ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ስላሉ ሁለንተናዊ የልማት እንቅሰቃሴዎች፣ በመልሶ ማቋቋሙ ስለተከናወኑ ተግባራትና ስለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዴንማርክ የኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት አጋር መሆኗን አመልክተው ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የልማትና ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ዳን ጀርገንስ በበኩላቸው በቅርቡ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰው ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የልማት ድጋፍ፣ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ረገድ አስፈላጊውን እገዛ እንደምታደርግ አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም የዴንማርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡

 

 

 

442 Views