ገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቀ

May 10, 2022

ግንቦት 2/ 2014 አዳማ ፡- ዛሬ በተጀመረው የፌዴራል እና የክልሎች የፋይናንስ አስተዳደር የምክክር መድረክ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል፡፡  

የምክክር መድረኩን የከፈቱት በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ወጪ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ሽመልስ እንደገለጹት በሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶችና በክልል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንዲደረግ በገንዘብ ሚኒስቴር የወጣውን የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር በሀገራችን ዘመናዊ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ከወረዳ ደረጃ ጀምሮ ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመልካም አስተዳደር መጎልበት እንደ አንድ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከወረዳ ጀምሮ የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት ተግባራዊ መደረጉ የዜጎች የመሰረታዊ አገልግሎቶች ቅድመ ፍላጎት በወረዳ ዕቅድ እንዲካተት በማድረግ፣ በበጀት አመዳደብና በወጪ አስተዳደር ተሳትፎ፣ በመሰረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ግምገማ፣ በመንግስት ግዥ አፈፃፀምና የኦዲት ግኝት መረጃዎችን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን አቶ ዳዊት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያ ቁጥር 51/2010 ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመመሪያው ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት፣ በዘርፉ የሰለጠኑ በባለሙያዎች ከስራ መልቀቅና መቀያየር ምክንያት ጉድለቶች ከመታየቸውም በላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ግጭትና አለመረጋጋት፣ የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን በቁርጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ  ያላስቻሉ ችግሮች እንደነበሩ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

1704 Views