ለመልሶ ማቋቋም የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተዘጋጀ

Dec. 27, 2021

በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስተር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ     ታህሳስ 15 2014 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመጀመሪያውን ውይይት ባደረገበት ወቅት ክቡር አቶ አህመድ እንደገለጹት በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ጠቁመው ተጨማሪውን በጀት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው በቀጥታ ወደ ስራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

መንግስት ከሚመድበው መነሻ በጀት በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተለይም ከአለም ባንክ ለመልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠበቅ ክቡር አቶ አህመድ ገልጸው የመልሶ ማቋቋሙ መርሀ ግብሩ በመንግስት የሚመራ፣ የተቀናጀ፣ በየደረጃው በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ ተጠያቂነት ያለውና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚተጋ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በጦርነቱና በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ለማውቅና በገንዘብ ለመተመን የሚያስችል የዳሰሳ ጥ ናት ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ ሀሳብ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለመልሶ ማቋቋም ሴክሬታያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የቀረበ ሲሆን የኮሚቴ አባላትም የመልሶ ማቋቋም መርሀግብሩ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች በተጨማሪ በሌሎች ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉትንም እንዲያካትት፣ የሀብት አሰባሰብ ድግግሞሽ እንዲወገድና በአንድ ቋት እንዲሰባሰብ፣ ክልሎች ንቁ ተሳትፎ የሚደርጉቡት ምቹ ሁኔታ እንዲመቻች፣ ከሌሎች መሰል ብሄራዊ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት እንዲሰራና የግሉን ዘርፍና ዲያስፖራውን እንዲያሳትፉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የስራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መስሪያ ቤት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡   

1800 Views