መንግስት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይ እርምጃ አንደሚወስድ ተገለጸ

March 16, 2022

 

መንግስት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይነት ያለው እርምጃ አንደሚወስድ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሸዴ ገለጹ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ዛሬ መጋቢት 7 / 2014 ዓ.ም በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት መንግስት በሰጠው አቅጣጫና የሀገሪቱ ብሄራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን በወሰነው መሰረት የኑሮ ውድነትን ለማሻሻልና ገበያውን ለማረጋጋት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጭ እንዲገባ ተወስኗል፡፡

በአሁኑ ጊዜም 12.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 4.8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለህብረተሰቡ እየተከፋፋለ ሲሆን 7.7 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ደግሞ በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ ተጠቃሎ እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ድፍድፍ ዘይት ከውጭ አስመጥተው በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ሶስት ፋብሪካዎችም ምርቶቻቸውን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ የውጭ ምንዛሬ የተመቻቻላቸው ሲሆን የምግብ ዘይት እጥረትን ለዘለቄታው ለመፍታትም እንዲቻልም ለሌሎች አቅራቢዎችም ዘይት ከውጭ አስመጥተው ለመንግስት እንዲሸጡ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡

መንግስት የኑሮ ወድነትን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት መንግስት የምግብ ዘይት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ በማድረጉ 23.7 ቢሊዮን ብር ያጣ ሲሆን ለነዳጅ የ100 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

1202 Views