በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የገንዘብ ሚኒስትሩ ገለጹ፡
May 9, 2022
ግንቦት 1/2014 ዓ.ም ዛሬ ቀጥሎ በዋለው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበጀት ስሚ መርሀ ግብር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የሚኒስቴሩ ተጠሪ መስሪያ ቤቶች የ2015 አመት የበጀት እቅዳቸውን አቅርበው በገንዘብ ሚኒስቴር ተገምግሟል፡፡
ግምገማውን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሰመዘገብ በሚደረገው ጥረት የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት በማሳደግ ረገድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የአረብ አገራት በህጋዊ መንገድ ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያን በመሄዱበት ሀገር ችግር እንዳይገጥማቸውና መሰረታዊ የቋንቋ፣የምግብ ዝግጅትና የቤት አያያዝ እውቀት ኖሯቸው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ለማድረግ የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም የማሰልጠኛ ተቋም የሚያስፈለጉትን ግብአቶችን ለይቶና አዘጋጅቶ ቢያቀረብ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ክቡር አህመድ አስረድተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የሆኑት የቴክኒክና ሙያ ስልጠናና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በገንዘብ ሚኒስቴር ከተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ በላይ የ2015 የበጀት እቅድ ያቀረቡ ሲሆን በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት ውስጥ በጀታቸውን አስተካክለው እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
ቀጥሎ በታየው የገቢዎች ሚንስቴርና የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ባለስልጣን በጀት ስሚ መርሀ ግብር ተቋማቱ በመደበኛ እና ካፒታል የበጀት መደቦች የጠየቁት በጀት ከተቀመጠው ጣሪያ በላይ በመሆኑ አስተካክለው እንዲያቀርቡና በመጪው በጀት ዓመት በገቢዎች ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂውን ለማሻሻልና የቢሮ ህንፃ ግንባታ የቅድመ ዝግጅት ስራን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን ያለበትን የተሸከርካሪ ችግር ለመቅርፍም ከሌሎች ተቋማት ጋር ጥቅል ግዢ ሰፈፀም አብሮ ምላሽ እንደሚያገኝ አቶ አህመድ ሽዴ ጨምረው አመልክተዋል፡፡