በግጭት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

June 15, 2022

ሰኔ 8 / 2014 ዓ.ም - በሀገሪቱ በግጭት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የተነደፈው ‹‹በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት›› ለባለድርሻ አካላት በስካይላት ሆቴል ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው መንግስት ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አሰታወቀ፡፡

‹‹በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት›› የልማት አጋሮች፣ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የክልል ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት መንግስት በግጭት የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

መንግስት ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የእለት ደራሽ እርዳታ በማቅረብ፣ ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ፣ በ2014 በጀት አመት ለመልሶ ማቋቋም የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በመመደብ እንዲሁም በ2015 በጀት አመት የ20 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ የመልሶ ማቋቋም ሂደቱ ውጤታማ አንዲሆን በትጋት ሲሰራ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ሁለት የትኩረት አቅጣጫዎች ጉዳት የደረሰባቸውን የህዝብ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባትና መሻሻል እንዲሁም ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎትና ድጋፍ መስጠት መሆኑን ክቡር አቶ አህመድ አመልክተዋል፡፡

የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በከፊል ኦሮሚያ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ክቡር ሚኒስትሩ ጠቅሰው የአለም ባንክን ጨምሮ የተባባሩት መንግስታት የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ (UNOPS)፣ የተባባሩት መንግስታ የህጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እንዲሁም ሌሎች የሁለትዮሽና አለም አቀፍ የልማት አጋሮች ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል፡፡

በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ተወካይ ሚስተር ኦስማን ዲዮን በበኩላቸው እንደገለጹት በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን የአለም ባንክ ከዚህ በፊት ያደርገው የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ አንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

914 Views