የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች ከአለም ባንክ ቦርድ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ጋር ባንኩ ለኢትዮጵያ ድጋፉን በሚያጠናክርበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

March 22, 2022

መጋቢት 13/ 2014 ዓ.ም - የአለም ባንክ የአፍሪካ ዳይሬክትር ዶ/ር ታውፊላ ንያማድዛቦ ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስተር ከአቶ አህመድ ሺዴ፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስተር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ፣ ከጤና ሚኒሰትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጋር የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ ስለሚጠናከርበትና በባንኩ ድጋፍ እየተከናወኑና ባሉና ወደፊት በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ፍሪያማ ውይይት አድርገዋል፡፡

ለባንኩ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ማለትም በኢኮኖሚ ማሻሻያው ስለተሰሩ ስራዎች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማዘመንና ለማሻሻል ስለተደረጉ ጥረቶች፣ የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቬስትመንት መስክ መሰማረት እንዲችሉ እየተሰጡ ስላሉ ድጋፎች፣ የግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይም በመስኖ የስንዴ ልማት ለማሳደግ እየተረደጉ ስላሉ ጥረቶች ውይይት ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታ ስለሚደረጉ ጥረቶች፣ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተሰጠ ስላለው ሰብአዊ አርዳታ፣ በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ የመገንባት ሂደት እንዲሁም ዘላቂ ሰላማችንና ልማታችን ለማረጋገጥ ብሄራዊ የምክር ኮሚሽን ስለመቋቋሙ ጥልቅ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የባንኩ ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ከገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይትም የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ የልማት አጋር መሆኑን አመልክተው ባንኩ ለመሰረተ ልማቶች ግንባታና ለመሰረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋት ለሚሰጠው ድጋፍና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ ሀገሪቱ በጦርንት፣ በድርቅና በኮቪድ የደረሰባትን ጉዳት ለመቋቋም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ክቡር አቶ አህመድ ጠቅሰው ከአለም አቀፉ የልማት ድርጅት የሚገኘው ውጭ ሀብት የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የመጠጥ ውሀና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋና ሀገሪቱ የነደፈችውን የ10 አመት መሪ የልማት እቅድ እውን ለማድርግ እንደሚረዳ ጨምረው ገልዋል፡፡

ዶ/ር ታውፊላ ንያማድዛቦ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዳይሬክተሩ ከሚመሩት 21 አባላት ካሉት የአፍሪካ ሀገሮች ቡድን አንዷ መሆኗን አመልክተው ኢትዮጵያ በግጭት፣ በድርቀና በኮቪድ 19 ጉዳት ውስጥ አልፋ አሁንም በልማት ጎዳና ለመራመድ የምታደርገውን ጥረት መገንዘባቸውን አመልክተው የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የአለም ባንክ በልማት አጋርነቱ እንደሚቀጥል አረጋጠዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ከመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች በተጨማሪም ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስት (ኢጋድ) እንዲሁም ከአፍሪካ ህበረት ዋና ጸሀፊዎች ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኙትን የሸገር፣ የእንጦጦና የአንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡ በዛሬውም እለትም ከገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴና ከሌሎች ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር በመሆን በየተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

1566 Views