የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሚተገበሩ ሶስት ፕሮጀክቶች የሚውል የ907 ሚሊዮን ዶላር የልማት ድጋፍ አደረገ

April 23, 2021

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 ዛሬ በገንዘብ ሚኒሰቴር በተደረገ የፊርማ ስነ-ሰርዓት ላይ በኢትዮጰያ መንግስት እና በዓለም ባንክ የ907 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሽዴና የዓለም ባንክ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚ/ር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመውታል፡፡ ስምምነቱ ሶስት አንኳር ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ይወላል፡፡

የመጀመሪያው የ200 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚውል ነው፡፡ ኢንተርፕራይዞች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ክፉኛ ተጎድተው ነገር ግን ቢደገፉ በስራቸው አዋጭ ሆነው ለመቀጠልና በንግድ ውስጥ እንዲቆዩ የሚያስችል ነው፡፡

የ500 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በሀገሪቱ ውስጥ ለሚከናወኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ተደራሽነት ከማሳደግ ባሻገር የግሉ ዘርፍ ካፒታል ተሳትፎን እና ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን ለማምጣት የሚያስችል አከባቢን ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ስምምነት ውስጥ 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚውለው የግሉ ዘርፍ በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ እና አቅርቦት ተሳትፎ እንዲኖረው ለማስቻል ነው፡፡

የመጨረሻው የ207 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያስከተለውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም የበሽታው መከላከያ ክትባቶችን ውጤታማ እና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረስ ለማድረግ የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ ነው፡፡

የስምምነቱ የተፈረመው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ክብረት ዶ/ር ሊያ ከበደ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ፍሬህይወት ወልደሃና፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው እና የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፊያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበእንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በተገኙበት ነው፡፡

1530 Views