የገንዘብ ሚኒስቴር ሁሉንም የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች በእኩልነት እንደሚያስተናግድ ይፋ አደረገ
Dec. 15, 2023
ታህሣሥ 5/2016 ዓ.ም - የገንዘብ ሚኒስቴር ከዩሮ ቦንድ አበዳሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ዓለም አቀፍ የኢንቨስተር ውይይት (Global Investor Call) አካሄዶ ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩል ሁኔታ እንደሚያስተናግድ ይፋ አደረገ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበይነ መረብ በተካሄደና ከ100 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ውይይት ስለሀገሪቱ ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ከልማት አጋሮችና ከውጪ አበዳሪዎች ጋር ስለተደረጉ የዕዳ ሽግሽግ ውይይቶች ማብራርያ አቅርበው ሀገሪቱ ከጋራ ማእቀፍ የዕዳ ሽግሽግ (Common Framework for debt treatment) ቀድሞ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ ለማድረግ ያላትን እቅድ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ከኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ጋር የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሷ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር የዩሮ ቦንድን ጨምሮ ከሌሎች የግል አበዳሪዎች ጋር ውይይት በመጀምር ሀገሪቷ ወጥነት ያለው የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግላት ጥረቱን ቀጥሏል።
በዚህ መሰረት ዶ/ር ኢዮብ የታህሣሥ ወር የዩሮ ቦንድ ወለድ ክፍያን ሀገሪቷ ላለመክፈል የወሰነችበትን ምክንያት አብራርተው ምንም አንኳን የክፍያ መጠኑ በአሁኑ የሀገሪቷ አቅም መከፈል የሚችል ቢሆንም ላለመክፈል የተወሰነው ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩል ሁኔታ ማሰተናገድ አስፈላጊ በመሆኑና ከሌሎች አበዳሪዎች ጋር እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶች እንዳያደናቅፉ የታለመ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ እቅድ የቦንድ ባላቤቶችን ከወዲሁ በማሳተፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የውጪ ብድር ችግሮችን መፍታት ሲሆነ ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ የጋራ ማእቀፍ የዕዳ ሽግሽግ (Common Framework for debt treatment) ውይይቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር እስኪሸጋገሩ ድረስ የቦንድ ባለቤቶችም የተሻለ የቦንድ ዋጋ ይዘው እንዲቆዩ የሚያስችል ነው።
ለዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች የቀረበው የዕዳ ሽግሽግ ምክረ ሀሳብ የተነደፈው የጋር ማእቀፍ የብድር ሸግሽግ ሲጀመር ሊያጋጥም የሚችለውን የድጋሚ ሽግሽግ ጥያቄ እንዳይፈጠር ታሳቢ በማድረግ ሲሆን ይህ ሽግሽግ መደረጉ በቦንዱ ባለቤቶች ላይ የሚያሳድረው ስጋት እንዳለ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚረዳ ሆኖ እነዚህን ስጋቶችን ለመቀነስም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሜ ገልጾ በግልጸኝነት፣ በተአማኒነትና በፍትሀዊነት መንፈስ ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር ለመወያየት ያለውን ዝግጁነት አሳውቋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ጥያቄ ፣ ሀሳብና አስተያየት አቅርበው ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በስፋትና በጥልቀት የተወያዩ ሲሆን ተጨማሪ ጥያቄዎች በቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ ያላቸውን አሰተያየት በኢሜል አድራሻ፡ eth.investors@lazard.com ላይ እነዲያቀርቡ ተጋብዘዋል።