መንግስት የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት በወሰደው እርምጃ ከሸቀጦች ታክስ ይገኝ የነበረ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ እንዳይሰበሰብ ቀሪ እንደተደረገ ተገለጸ

May 18, 2022

ግንቦት 10 / 2014 . - የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ያለፉት ዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሲገመገም እንደተገለጸው መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የምግብ ሸቀጦች ያለውጪ ምንዛሪ (በፍራንኮ ቫሉታ) እንዲገቡ በመደረጋቸውና በምግብ ሸቀጦች ላይ ጥሎት የነበረውን ታክስና ቀረጥ በማንሳቱ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሳይሰበሰብ ቀሪ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡

የስንዴ ዋጋን ለማረጋገትና ዋጋው በጣም ከፍ እንዳይል ለማድረግ በተደረገውም ጥረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 320 ቶን ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን የምግብ ዘይትን በተመለከተም ገበያውን ለማረጋጋት የምግብ ዘይት ግዢ ውል መፈጸሙም ታውቋል፡፡

የፌዴራል መንግስት የበጀት ጉድለትን ለማጥበብና የሀገር ወስጥ ብድር እንዳይጨምር ለማድረግ በተወሰደው እርምጃም ከመደበኛ በጀት 5 ቢሊዮን ብር የወጪ ቅነሳ የተደረገ ሲሆን 26 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች ወደሚቀጥለው በጀት አመት እንዲዛወሩ መደረጋቸው ከዘጠኝ ወራቱ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖረት ለማወቅ ተችሏል፡፡

የውጭ ሀብት ለማሰባሰብ በተደረገውም ጥረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ቢሊዮን ዶላር በብድርና በእርዳት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲፈስ ታቅዶ በዚሁ ወቅት 2.26 ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ የፈሰሰ ሲሆን አፈጻጸሙም 111.1 በመቶ ሊሆን ችሏል፡፡

የእዳ ክፍያን በተመለከተም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ብድር 24.9 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ 20.7 ቢሊዮብ ብር ክፍያ እንደተፈጸመና አፈጻጸሙም 83 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሀገር ወስጥ እዳ ክፍያ በተመለከተም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 10.4 ቢሊዮን ብር የሀገር ውስጥ ብድርን ለመክፈል ታቅዶ 17 ቢሊዮን ብር እዳ ክፍያ የተፈጸመ ሲሆን አፈጻጸሙም 164.2 በመቶ ሆኗል፡፡

የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማውን የመሩት የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት በገንዘብ ሚኒስቴርና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ በሆኑ ተቋማት በዕቅዱ መሰረት ያልተከናወኑ ተግባራትን በመለየት በቀሪው ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አመልክተው ደካማ ጎኖችን ማረምና ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ የእቅድ አፈጻጸምን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በግምገማው ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተጨማሪ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆኑት የመንግሰት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ የመንግስት ግዢ ባለስልጣን እንዲሁም የመንግስት ግዢ አገልግሎት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀማቸው ቀርቦ ግምገማና ውይይት ተደርጎበታል፡፡

694 Views