በኢትዮጵያ ፕሮጀክት በጋራ መቆማችንን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ

Jan. 13, 2022

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ለተሰኘች ውብ ፕሮጀክት እውን መሆን በጋራ መቆም አንደሚገባውና ለልጆቻችን የተሸለች ኢትዮጵያን ማውረስ እንደሚጠበቅብን የገንዘብ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካለኝ ገለጹ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ መስሪያ ቤቶች አመራሮችና ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጥር 4 2014 ዓ.ም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገ ውይይት ላይ ዶ/ር እዮብ አንደገለጹት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለአንድ አላማ የሚያሰልፍ ኢትዮጵያ የተባለች ውብ ፕሮጀክት አንዳለችንንና ሰላሟና ልማቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማውረስም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጋራና በጽናት መቆም እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

እስካሁን የተገኙትን ድሎችን አሳንሶ ከማየት ይልቅ የጋራ ድላችን አድርገን መቀበልና ለፍጻሜው ድል ተግቶ መሰለፍ እንደሚገባ አመልክተው ከድል በኋላ የሚመጡ ተግዳሮቶችን በሚገባ እየፈቱ መሄድና የድህረ- ጦርነት መዛነፎችን እያስተካከሉ በእድገትና ልማት ጎዳና ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው ለሁላችንም ያለችን አንዲት ሀገር ኢትዮጵያ በመሆኗ ለሀገር ከምናበረክተው አስተዋጽኦ አኳያ ከያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል የሚለውን አጢነን የዜግነታችን ግዴታ መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡

በወይይቱ እንከተለው የነበረ የፖለቲካ ስርአት ባስከተለብን አሉታዊ ተጽእኖ፣ በህግ የበላይነትን ማስፈን፣ በሀገራዊ የምክክር መድረክ፣ በህገ-መንግስት ጉዳዮች፣ በግለሰብና በቡድን መብት፣ በመልሶ ማቋቋም፣ በዘላቂ ሰላም የለማስፈንና በሌሎችም ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከመድረኩም ጥልቀት ያለው ምላሽና ማብራሪ ተሰጥቷል

832 Views