ኢትዮጵያና ስፔን የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ
Feb. 16, 2023
የካቲት 9/ 2015 ዓ.ም - የኢትዮጵያና የስፔን መንግስታት በቀጣይ አምስት ዓመት የኢኮኖሚ ትብብራቸው የሚመራበትን ማዕቀፍ የገንዘብ ሚንስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴና የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴ ማንኤል አልባሬስ ቤኖ በገንዘብ ሚንስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈራረሙ፡፡
የማዕቀፍ ስምምነቱን የፈረሙት ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያና ስፔን ረጅም ጊዜ ያሰቆጠረ ግንኙነት እንዳለቸው አስተውሰው በአሁን ወቅት የስፔን መንግስት በዓለም አቀፍ የጤና ተደራሽነት፣ በአካታች የገጠር ልማትና በስርዓተ ፆታ ዕኩልነት እያበረከተ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
ባለፋት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ነድፎ ዘላቂነት ያለው ፈጣን ልማት ለማምጣት፣ የግሉ ዘርፍ በየኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲጎለብትና አዳዲስና ነባር የኢንቨስትንት መስኮች እንዲስፋፉ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆሴ ማንኤል አልባሬስ ቤኖ በበኩላቸው አዲስ የተፈረመው የአምስት አመታታ የትብብር ማዕቀፍ የኢትዮጵያና የስፔንን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸው ስፔን አለም አቀፉን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከመንግስታት ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደምትገኝ አስተውሰዋል፡፡
አሁን የተፈረመው የአምስት አመታታ የትብብር ማዕቀፍም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በጤና፣ በገጠር ልማት፣ በስርዓተ ፆታ ዕኩልነትና በሰብዓዊ ድጋፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንደሚያጠናክርም ሆሴ ማኑኤል ጨምረው አስረድተዋል፡፡