ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ሀይል ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

March 4, 2022

የካቲት 25 / 2014 ዓ.ም - በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት በተሰጠው የኢነርጂ ዘርፍ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ሀይል ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የ2014 በጀት አመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ዛሬ በሂልተን ሆቴል በገንዘብ ሚኒስቴርና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በተገመገመበት ወቅት ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ እንደገለጹት መንግስት ለኢነርጂ ሴክተር ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው በመሆኑ በጥንቃቄ የሚከታተለውና የሚመራው ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡

በሀይል ማመንጨትና ማሰረጫት ዘርፍ ያለው የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና የዘርፉ የፕሮጀክት አመራርና አፈጻጸም ትኩረት ሊሰጠው አንደሚገባው ሚኒስትሩ አመልክተው በሁለቱም ተቋማት በኩል ከደንበኞች ያልተሰበሰበው ገንዘብ በጊዜ እንዲሰበሰብ በተለይም ወደ ጎረቤት ሀገሮች ከተላከው ሀይል ያልተሰበሰበውን ገንዘብ ተከታትሎ ገቢ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የሀይል ብክነትንና መቆራረጥን መቆጣጠር፣ ወጪ ቅነሳን ተግባራዊ ማድረግ፣ በክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የዘርፉን ያልተማከለ አስተዳደር አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ክቡር አቶ አህመድ ጠቁመው ገንዘብ ሚኒስቴርም ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ ለተቋማቱ እነደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በግምገማ መድረኩ ባቀረበው ሪፖርት ባለፉት ስድስት ወራት የደንበኞቹ ቁጥር 4.1 ሚሊዮን መድረሳቸውን አመልክቶ በዚሁ ወቅት ለ176ሺ አዳዲስ ደንበኞች ኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉንና የኤክትሪክ ሀይል ሽፋኑም 48 በመቶ መድረሱን አስረድቷል፡፡

በበጀት አመቱ ግማሽ አመት ለ81 አዳዲስ ቀበሌዎችና ከተሞች የኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት መስጠቱን ይፋ ያደረገው ተቋሙ ከአገልግሎት ክፍያ 8.9 ቢሊዮን ብር ገቢ እንዳገኘና ይህም የእቅዱ 83 በመቶ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጡ ቅሬታ የሚቀርብበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳዲስ ደንበኞችን ለማስተናገድ ያስቀመጠው የ15 ቀን የጊዜ እርዝማኔ በተግባር ግን 102 ቀናት መፍጀቱና የደንበኞችን ቅሬታ ለመፍታት ያስቀመጠው 25 ቀናት 75 ቀናት መፍጀቱ በግምገማው ወቅት እንደ ድክመት ተጠቅሶ ይህን ችግር እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የግማሽ አመት የስራ አፈጻጸሙ የተገመገመው ሌላኛው ተቋም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሀይል ምንጭ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 17 የሀይል ማመንጫዎችን እያስተዳደረና የኤሌክትሪክ ሀይል ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለጅቡቲና ለሱዳን እያቀረበ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትክ ሀይል በግማሽ አመቱ የ7.6 ቢሊዮን ብር ገቢና የኤሌክትሪክ ሀይል ለጅቡቲና ለሱዳን በመሸጥ 46 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሶ የህዳሴውና የኮይሻ ሀይል ማመንጫ ግድቦች ከፍጻሜ እንዲደርሱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አሰረድቷል፡፡

1317 Views