ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተሰማሙ
March 17, 2021በገንዘብ ሚኒስትር በክቡር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጂቡቲ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከክቡር ራድዋን አብዲላሂ ባህዶን በጂቡቲ የፖስታ እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው ውይይት አካሂደዋል፡፡ ሁለቱ አገራት በቴሌኮሙኒኬሽን መስክ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ላይም ተመካክረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒሰቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮምን ዘርፍን ለማሻሻል እየወሰደ ስላለው እርምጃ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተለይም ሁለት አለምአቀፍ ኩባንያዎች በቴሌኮም ኦፕሬተርነት እንዲሳተፉ ጨረታ መውጣቱንና ጨረታውም እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 5 ቀን 2021 እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው ሂደትም በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን አሳይተዋል ብለዋል፡፡በተመሳሳይ ሁኔታም ኢትዮ-ቴሌኮም ስትራቴጂካዊ አጋር እንዲኖረው ያለው ድርሻ 40 በመቶ ለሽያጭ እንዲያቀርብ መንግስት መወሰኑንና ለዚህም የዝግጅት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ እያደገ በሚመጣበት ወቅት ጂቡቲ በቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት ይበልጥ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንደምትሆንና በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የቴሌኮም ትራፊክ ደህንነት በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ ጂቡቲ ወሳኝ ሚና ይኖራታል ሲሉ ሚኒስትሩ ገለፀዋል ፡፡
በጂቡቲ የፖስታ እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒሰቴር ሚኒስትር ራድዋን አብዲላሂ ባህዶን በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የጂቡቲ መንግስት የቴሌኮም ዘርፍን በማጠናከርና በማዘመን የምስራቅ አፍሪካን የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሁለቱ አገራትም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡