ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትብብር እንደሚፈጥር ተገለጸ

Jan. 3, 2024

ታህሣሥ 24 / 2016 ዓ.ም - ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ወታደራዊ የባህር ሀይል ቤዝና የኮሜርሺል ማሪታይም አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበት የመግባቢያ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትብብር እና ትስስር የሚፈጥር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ገለጹ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ወታደራዊ የባህር ሀይል ቤዝና የኮሜርሺል ማሪታይም አገልግሎት ለረዥም ጊዜ በሊዝ መጠቀም የሚያስችል የመግባበቢያ ሰነድ በተመለከተ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት እንዳብራሩት ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እንዲለሙ ከማድረጉም በላይ በቀጠናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር በመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ጋር የጀመረችው ኢኮኖያዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ይህን ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚያስተናግድ የወደብና የሎጂስቲክ ግንኙነት ከጅቡቲ፣ ከኬንያና ከሌሎችም አገሮች ጋር እንደሚቀጥል እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሩና ትብብሩ እየዳበረ እንደሚሄድ ክቡር ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ይህ የመግባቢያ ስምምነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርቶ ዝርዝር አፈጻጸሙ በሚቀጥለው አንድ ወር  የሚተገበር ሲሆን በአጠቃላይ ለባህር ያለን ተደራሽነት በማሳደግ፣ በኤደን ሰርጥ የሚኖረን ተሳትፎ በመጨመር፣ ታሪካዊ ግንኙነታችንን በማጠናከር፣ ደህንነታችንን በማስጠበቅ፣ የወል እውነትን እና ትርክትን በማሳደግ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውና  ከቀጠናዊ ትስስር እና የመሰረተ - ልማት ዝርጋታ አንጻርም ኢኮኖሚያችንን በሚያሳድግ መልኩ ለወደቡ ተደራሽነት በሚሰሩ ስራዎች ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር  ክቡር ሚኒስትሩ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የዜጎች የዘመናት ቁጭት የሆነው የወደብ ጉዳይ ይህን በመሰለ ሰላማዊ መንገድ እውን በመሆኑ እንኳን ደስ ያለን ካሉ በኋላ በህጋዊ መንገድ የወደብ ባለቤትና ተጠቃሚ መሆናችን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ ጥቅም ያለው በመሆኑ ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሰራተኞችም በዚህ ለረዥም ጊዜ በቁጭትና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ሃገራዊ አጀንዳ እውን መሆን ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

2108 Views