ከ43 ሚሊዮን ሊትር በላይ የፓልም የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ

Jan. 3, 2023

 

ታህሣሥ 25 / 2015 ዓ.ም - ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ ዘይት አንዲያገኝ በጅቡቲ ከሚገኘው ጎልደን አፍሪካ ካምፓኒ የ43 ሚሊዮን 37 ሺ 412 ሊትር የፓልም የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አሰታውቋል፡፡

የግዢ ውሉን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ሲሆኑ ለግዢ የሚውለውን የ69 ሚሊዮን 894ሺ 440 የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋትና የሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑ ታወቋል፡፡

የምግብ ዘይቱ ግዢ በአንድ አመት የክፍያ ጊዜ የሚፈጸም ሲሆን ይህን የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ዋጋን ለማረጋጋት ታስቦ የተፈጸመውን ግዢ ያስተባባረው የገንዘብ ሚኒስቴር የግዢ ውሉን ለተፈራራሙት ለኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅቶች በላከው ደብዳቤ በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ እሽግ የፓልም ምግብ ዘይት የመሸጫ ዋጋ እንደሚከተለው አሳውቋል፡-

በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ የፓልም ምግብ ዘይት መሸጫ ዋጋ

  • ባለ 3 ሊትር በጄሪካን …… ብር 314
  • ባለ 5 ሊትር በጄሪካን …… ብር 510
  • ባለ 20 ሊትር በጄሪካን …… ብር 2003 መሆኑ ታውቋል

ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ከተሞችን በተመለከተም ርቀትን ታሳቢ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ታሪፍ በኩንታል 60 ሳንቲም በአንድ ኪ.ሜ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ ሽያጭ እንዲከናወንና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በተለመደው መልኩ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን የስርጭት ኮታ በመመደብ ለኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት እዲያሳውቅ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

472 Views