የሀገራዊ ሀብት አስተባባሪ ኮሚቴ የአመቱ የስራ አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር ተገለጸ
Sept. 7, 2022
ጷጉሜ 2 / 2014 ዓ.ም - ሀገራዊ ሀብት አስተባባሪ ኮሚቴ በዚህ አመት ከውጭ ሀገርና ከሀገር ውስጥ ሀብት በማሰባሰብ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በመርዳትና መልሶ በማቋቋም የተከናወነው ተግባር ውጤታማ እንደነበር ገምግሟል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ የተቋቋመው ሀገራዊ የሀብት አስተባባሪ ኮሚቴ የ2014 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀብት በማሰባሰብ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም በተደረገው ጥረት የእለት ደራሽ እርዳታ ከማቅረብ ጀምሮ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀደመ አካባቢያቸው በመመለስ እንዲቋቋሙ መጠነ ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በዚህም መሰረት ኮሚቴው በተለይም ከውጭ ሀብት ለማሰባሰብ ባደረገው ጥረት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አማካኝነት የዶላር፣ የዩሮና የፓውንድ የውጭ ምንዛሬ የባንክ ሂሳቦች በመክፈት ከመላው አለም ከሚገኙ ኢትዮጵዊያንና ትውልደ ኢትዮጵዊያን ያሰባሰበውን 7 ሚሊዮን ዶላር ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገቢ ማድረጉም ተገልፆል፡፡
የአደጋ ስጋት አመራራ ኮሚሽን በበኩሉ ‹‹ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ›› በሚል ስያሜ በከፈተው የባንክ ሂሳብ ገቢ የተደረገለትን 7 ሚሊዮን ዶላር (355.6 ሚሊዮን ብር) ዝርዝር የአፈጻጸም የድርጊት መርሀ ግብር በማውጣት በመላው ኢትዮጵያ በግጭት፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከእለት ደራሽ እርዳታ ጀምሮ የሰብአዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ተግባር ሲያከናውን መቆየቱም ታውቋል፡፡
ይህ ከመላው አለም ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵዊያንና ትውልደ ኢትዮጵዊያን የተሰባሰበው ገንዘብ ሀገራዊ የሀብት አስተባበሪ ኮሚቴ በሰጠው አመራርና ጥብቅ ክትትል ለታለመለት አላማ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንም ገንዘቡን በአግባቡ ስራ ላይ ስለማዋሉ በፋይናንስ አስተዳደር አዋጁ መሰረት ለገንዘብ ሚኒስቴር የሂሳብ ሪፖርት እያቀረበ ስራው ሲከናወን መቆየቱም ተመልክቷል፡፡
በዚህም መሰረት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገቢ ከተደረገለት 355.6 ሚሊዮን ብር ውስጥ 235.8 ሚሊዮን ብር ለታለመለት አላማ ወጪ አድርጎ 119.7 ሚሊዮን ብር ከወጪ ቀሪ እንዳለ ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
በውጭ ምንዛሬ ከተሰበሰበውም ገንዘብ ውስጥ 261ሺ 841 ዩሮና 994ሺ 587 ዶላር ቀሪ ገንዘብ አሁንም በባንክ ውስጥ ያለ ሲሆን ከውጭ ለዜጎች ድጋፍ የሚሰበሰበው ሀብት በመንግስት የፋይናንስ አስተዳዳር አዋጅ መሰረት የመንግስትን የባንክ ሂሳብ ለመክፈት ስልጣን በተሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት ተግባራዊ የተደረገና ወጪውም ለታለመለት አላማ ስለመዋሉ በሂሳብ ሪፖርት እየተረጋገጠ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገበት ሰለመሆኑ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡
በዚህ ወቅትም የልማት ሥራዎችና ፕሮጀክቶች እንዳይቆሙ፣ የመልሶ ማቋቋም እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲቀላጠፉና ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲዳረስ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵዊያንና ትውልደ ኢትዮጵዊያን ለድጋፍ በተከፈቱት የባንክ አካውንቶች ማለትም
- EURO- 1000439142832 (ዩሮ)
- USD- 1000439142786 (ዶላር)
- GBP- 1000443606304 (ፓውንድ)
ሀገራቸውን እንዲረዱ ሀገራዊ የሀብት አስተባባሪ ኮሚቴ በድጋሚ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡