የመሬት መራቆትን በመቀንስ ምርታማነትን ለሚያሻሽል ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ165.2 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታና የብድር ስምምነት ተፈረመ

Aug. 10, 2022

 

ነሐሴ 4 / 2014 ዓ.ም - የመሬት መራቆትን በመቀንስ ምርታማነትን ለሚያሻሽል የዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ165.2 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታና የብድር ስምምነት በኢትዮጵያ መንግስትና በአለም ባንክ መካከል በበይነ መረብ በተካሄደ ስነ-ስርአት ተፈረመ፡፡

የዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች፣ በ170 ወረዳዎችና በ217 ተፋሰሶች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ዘላቂ የመሬት አያያዝ ሥራዎችን ወጥና ተደጋጋፊ በማድረግና ውጤታማ የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅና አጠቃቀም ልምዶችንና ሥርዓትን በማስፋፋት በ789ሺ ቤተሰቦች ውስጥ የታቀፉ 4 ሚሊዮን ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረጋል፡፡

ዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ በመሬት አያያዝ ዙሪያ የማህበረሰብ እና የተቋም ግንባታ፣ በተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድና በአርሶ አደሩ የይዞታ ማረጋገጫ ሠርተፊኬት አሰጣጥና በፕሮጀክት አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ሲሆን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን አርሶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያከናወናል፡፡

 

ይህ በግሪን ክላይሜት ፈንድ (GCF) በተገኘ የገንዘብ ምንጭ በዓለም ባንክ በኩል ተግባራዊ ከሚደረገው የዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም በጀት ውስጥ 58 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ሲሆን 107 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በረጅም ጊዜ የሚከፈል እጅግ ቀላል ብድር መሆኑ ታወቋል፡፡

 

ዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም የ15 ዓመት ስትራቴጂክ የኢንቨስትመንት ማእቀፍ እ.ኤ.አ በ2008 የተጀመረና በሶስት ምእራፎች ተከፋፍሎ  እ.ኤ.አ  በ 2024 የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ሲሆን የፕሮጀክቱ ዓላማ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ በመስራት የመሬት መራቆትን በመቀነስ እንዲሁም የመሬት ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል ነው፡፡

የገንዘብ ድጋፍ ስምምቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የፈረሙ ሲሆን በአለም ባንክን በኩል ግሪን ክላይሜት ፈንድን በመወከል ደግሞ አቶ አሳዬ ለገሰ ፈርመዋል፡፡

 

 

 

 

882 Views