የኦዲት ግኝት የተመዘገበባቸው 39 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በገንዘብ እንዲቀጡና ከባድ የጽሁፍ የማሰጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲጻፍባቸው ተወሰነ
April 20, 2022ሚያዝያ 12 / 2014 ዓ.ም - በዋና ኦዲተር ባለፉት ሶስት አመታት ተመርምረው የኦዲት ግኝት የተመዘገበባቸው የ9 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበላይ ሀላፊዎችና የፋይናንስ ዳይሬክተሮች እያንዳንዳቸው በቅደም ተከተል 10ሺ እና 9ሺ ብር እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ሲሆን በሌሎች 30 ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ደግሞ ከባድ የጽኁፍ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲጻፍባቸው ተወስኖ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
የገንዘብ ቅጣቱ የተወሰነባቸው የአሶሳ፣ የቡሌ ሆራ፣ የደብረማርቆስ፣ የኦዳ ቡልቱ፣ የባህር ዳር፣ የሲቪል ሰርቪስ፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዚዳንቶችና የፋይናንስ ዳይሬክተሮች ሲሆኑ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የበላይ ሀላፊዎችና የፋይናንስ ዳይሬክተሮችም የገንዘብ ቅጣቱ ከተወሰነባቸው ተቋማት መካከል ይገኙበታል፡፡
ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም ባሉት ሶስት አመታት ውስጥ ሂሳባቸው የጎላ ችግር ያለበት በመሆኑ ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተየያት የተሰጣቸውና ሂሳባቸውን አይቶ አስተያየት መስጠት ያልተቻለበት የእነዚህ 39 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ሀላፊዎችና ተቋማት ላይ እርምጃ የተወሰደው “የፋይናንስ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት የሚወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መመሪያ ቁጥር 48/2009›› መሰረት ነው፡፡
በዚህ መመሪያ አንቀጽ 15.1 መሰረት በማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የተሾመ ወይም የተመደበ ሰው በመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ፤ በአዋጁ መሰረት በወጡት ደንቦችና መመሪያዎች መሰረት በህግ የተወሰነውን ሀላፊነትን ባለመወጣቱ ምክንያት በዚህ መመሪያ ከሶስት ጊዜ በላይ ቅጣት ከተጣለበት ከሀላፊነት እንዲነሳ ሊደረግ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
የገንዘብ ቅጣት ከተላለፈባቸው ዘጠኝ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበላይ ሀላፊዎችና የፋይናንስ ዳይሬክተሮች ውስጥ ሰባቱ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶችና የፋይናነስ ዳይሬክተሮች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የሌላ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የበላይ ሀላፊዎችና የፋይናንስ ዳይሬክተሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡