የገንዘብ ሚኒስቴር ግምታቸው 2 ሚሊዮን ብር የሚሆኑ ግብአቶችን ለመቄዶንያ የአዕምሮና አረጋዊያን መርጃ ማዕከል በሰጦታ አበረከተ
June 28, 2021
ሰኔ 08 ቀን 2013 ዓ.ም፡- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ገንዘብ ሚኒስቴር አጠቃላይ ግምታቸው ወደ 2 ሚሊዮን ብር የሚሆኑ የኮንስትራከሽን፣የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችን፣የተሸከርካሪ ጎማዎችንና ምንጣፍ ግብአቶችን ለመቄዶንያ የአዕምሮና አረጋዊያን መርጃ ማዕከል በዛሬው ዕለት በስጦታ አበረከተ፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ት ያስሚን ወሀብረቢ የርክክብ ስነ ስርዓቱ በተካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት መንግስት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገልገል የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀው በዛሬው ዕለትም የገንዘብ ሚኒስቴር የአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን ያለባቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚረዳ ግምታቸው ከ1.5 እስከ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ቁሳቁሶችን ለመቄዶኒያ የአዕምሮና አረጋዊያን መርጃ ማዕከል እንዳበረከተ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ አያይዘውም የመርጃ ማዕከሉ ከ5000 በላይ የሚሆኑ አረጋዊያንንና የአዕምሮ ህሙማንን ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሰው ይህንን አበረታች ተግባር ከመደገፍ አኳያ ማመስገን ብቻ ሳይሆን መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
መቄዶኒያ ”ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው“ በሚል መሪ ቃል በጀመረው ስራ ላይ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊተባበር ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ መሪ ቃሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም ላይ ለሚኖር ማኛውም ማህበረሰብ ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል ጨምረው አስገንዝበዋል፡፡
የመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠም በበኩላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር የተለያዩ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ከመቄዶንያ ጎን በመሆን የተለያዩ እገዛዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በዛሬው ዕለት የተደረገው ስጦታ ደግሞ ማዕከሉ በ1.3 ቢሊዮን ብር እያስገነባ ላለው ባለ ሁለት ቤዝመንት አስራ ሁለት ፎቅ ህንጻ ግንባታ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም ማዕከሉ በሀረር፣ በጎሬ፣ በአድዋ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከመንግስት የህንጻ ግንባታ ቦታዎችን ተቀብሎ ግንባታ የጀመረና በቀጣይ ከጎዳና በማንሳት አገልግሎት ሊሰጣቸው ካቀደው ከ6000 በላይ ለሚሆኑ አረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን ተረጂዎች የዛሬው ልገሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በአሁኑ ጊዜ በቀን እስከ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ አለበት ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ ዛሬ በገንዘብ ሚኒስቴር የተደረገው እገዛ ያሉባቸውን ችግሮች ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው በቀጣይም መንግስት ከጎናቸው ሆኖ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ በመልዕክታቸው አስተላልፈዋል፡፡