የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አሰታወቁ
April 9, 2022
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በደቡብ ሱዳን የገንዘብና ፕላን ሚኒስትር አጋክ አቹል የተመራ ልዑክ በተቀበሉበት ወቅት ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በውይይቱ እንደተገለፀው በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ የሚንስትሮች ኮሚቴ እንዲዋቀር ይደረጋል ተብሏል፡፡
ሀገራቱ በኮሚሳ እና በኢጋድ እንዲሁም በአለም አቀፍ ተቋማት መካከል በሚደረጉ ግንኙነቶች ማለትም በፋይናንስ እና በቴክኒክ በጋራ ለመሰራት ተሰማምተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት ሁለቱ እህትማማች ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸው በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በተለይም ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በጉምሩክ ብሎም በመሰረተ ልማት ማለትም በመንገድ፣በሃይል አቅርቦት በትብብርና በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣይም ለደቡብ ሱዳን አንድነትና ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሏን አሰተዋፆ እንደምታበረክትም ገልጸዋል፡፡
በሀገራቱ መካከል በመሰረተ ልማት ዘርፍ እያተደረጉ ያሉ ግንኙነቶች የነዳጅ ግዢና ሽያጭ እንዲቀላጠፍ ብሎም ደቡብ ሱዳን የጅቡቲን ወደብ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በማህበራዊ፣በኢኮኖሚ እና በፓለቲካዊ መስኮች ማሻሻያዎች እያደረገች መሆኑን ለከፍተኛ ልዑካን አሰረድተዋል፡፡
በተለይም የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ሚና ለማሳደግ እየተሰራ ሲሆን የቴሌኮም ዘርፍ ወደ ግል የማዞር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ በባንኩ ዘርፍ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች እንዲሳተፉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን አቶ አህመድ ሽዴ ገልፀዋል፡፡
የገንዘብና ፕላን ሚኒስትር አጋክ አቹል በበኩላቸው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን በኢኮኖሚ ፣ በሰላምና ደህንነት እያደረገች ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድንቀዋል ፡፡ በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ የሚንስትሮች የጋራ ኮሜቴ መዋቀሩን አወድሰዋል፡