የፌዴራልና የክልሎች የፋይናንስ፣ የገቢዎችና የፕላን የጋራ ምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ተጀመረ

Dec. 19, 2022

ታህሣሥ 8 / 2015 ዓ.ም - በሀገራዊ የልማት እቅድ፣ በፊሲካል ፖሊሲ፣ በመንግስት ወጪና ገቢ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የፌዴራልና የክልሎች የፋይናንስ፣ የገቢዎችና የፕላን መስሪያቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተጀመረ፡፡

የምክክር መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት የምክክር መድረኩ አላማ በሀገራዊ የልማት እቅድ፣ በፊሲካል ፖሊሲ፣ በመንግስት ወጪና ገቢ አፈጻጸም ረገድ ያጋጠሙ ችግሮች ላይ በጋራ በመምከር የወደፊት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው፡፡

ባለፉት ሶስት አመታት በፊስካል ፖሊሲ አፈጻጻም፣ በገቢ አሰባሰብና በወጪ አፈጻጸም ረገድ የተለያዩ ችግሮች የተስተዋሉ መሆናቸውን አመልክተው የፊሲካል ፖሊሲው ዋና ግብ ከኢኮኖሚው እድገት አንጻር ሊገኝ የሚችለውን የመንግስት ገቢ በመሰብሰብ ወጪውን መሸፈን አንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የታክስ ገቢ ከሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ጥምርታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ ምክንያት መንግስት ከኢኮኖሚ እድገቱ ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ እየሰበሰበ አለመሆኑን ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ጠቅሰው ይህም እየጨመረ የመጣውን የመንግስት ወጪ ፍላጎት ካለመሸፈኑም በላይ የበጀት ጉድለቱ እንዲሰፋ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ስለዚህም ከዚህ የፌዴራልና የክልሎች የፋይናስ፣ የገቢዎችና የፕላን የጋራ ምክክር መድረክ ሀገራዊ የልማት እቅዱን በማስፈጸም፣ የታክስ አስተዳደር ስርአትን በማጠናከር ገቢን በማሰባሰብና በማሳደግ፣ ስራ ላይ ያልዋሉትን የታክስ ህጎች በማውጣትና በመተግበር፣ ወጪን በአግባቡና በቁጠባ በመጠቀምና የፋይናንስ አስተዳደር ስርአትን በማሻሻል ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

804 Views