ዳያስፖራው ለሀገሩ
Sept. 6, 2021ዲያስፖራው በእውቀቱና በገንዘቡ ለሀገሩ በርካታ አስተዋጽዎ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በህልውና አደጋ ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ፈታኝ ወቅትም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ሀገራቸውን ገዕታ በመገንባት፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማስተባበል፣ በሚኖሩባቸው ሀገራት የሚገኙ መንግስታት ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያራምዱትን ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር፣ በኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍና በመደገፍ ለወገንና ለሀገር አለኝታ በመሆን ውድ ሀገራቸውን ከጥፋት መታደግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ለሀገራቸውም የፅናት ምንጭ በመሆን ደጀንነታቸውን እያሳዩና የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመላው አለም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ይኖራሉ፡፡ እነዚህ በውጭ ሀገራት የሚኖሩት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ዶላርም ሆነ ሌሎች የውጭ ምንዛሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ቤተሰባቸውን ለማገዝና በሀገር ቤት ለሚያከናውኑት ተግባር ይልካሉ፡፡ ታዲያ ከሚላከውም የውጭ ምንዛሪ የሚበዛው በህጋዊ መንገድ በባንክ እንደማይላክም ይታወቃል፡፡
በህጋዊ መንገድ የማይላከው የውጭ ገንዘብ ሀገራችንን በተለያየ መልኩ ጉዳት እያደረሰባት ነው፡፡ ስለዚህም ሀገር ወዳድ ዲያስፖራዎች በዚህ ፈታኝ ወቅት መላ ሊመቱ ይገባል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ኢትዮጵያን ለማዳን በጦር ሜዳ እየተዋደቁ ሲሆን ሌሎች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ደግሞ የውስጥና የውጭ አፍራሽ ሀይሎችን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመመከት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱ ግንባር ማለትም የጦርና የፕሮፓጋንዳ ግንባሩ እየተመከተ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ደግሞ ሶስተኛ ግንባር ተከፍቶብናል፡፡
ይህም ግንባር የኢኮኖሚ አሻጥር ግንባር ነው፡፡ የኢኮኖሚ አሻጥሩ አንደኛው መገለጫ ሀገሪቱ ዶላርና ሌሎች የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝና ያገኘችውንም በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ ይህን አሻጥር በመመከት ረገድ ከዲያስፖራው ብዙ ይጠበቃል፡፡ እርግጥ ነው ዲያስፖራው በሀገሩ ኢንቨስት በማድረግ፣ የህዳሴ ግድቡን ቦንድ በመግዛት፣ የተለያዩ ሰብአዊ እርዳታዎችን በማድረግና የተቸገሩ ወዳጅ ዘመዶቹን በመርዳትና በማቋቋም አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ ለዚህም ተሳትፎው ከልብ ሊመሰገን ይገባል፡፡
የኢኮኖሚ አሻጥሩን ከመመከት ብሎም የኢትዮጵያን ህልውና ከማስቀጥል አኳያ በዚህ ፈታኝ ወቅት ከሀገር ወዳዱ ኢትየጵያዊ ዲያስፖራ ከምን ጊዜውም በበለጠ ሁኔታ አስተዋጽኦው የሚጠበቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ወቅት ‹‹ዶላር ለሀገሬ›› በሚል መርህ እያንዳንዱ ዲያስፖራ ወደ ኢትዮጵያ የሚልከውን ዶላርና ሌሎች የውጭ ምንዛሬዎችን በህጋዊ መንገድ በባንክ ቢልክ ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ እንደዋለላት ይቆጠራል፡፡
የሀገር ህልውና የማስጠበቁ ተግባር በጦር ሜዳ ብቻ በሚካሄደው ተጋድሎ አይረጋገጥምና ሀገር ወዳዱ ዲያስፖራ ለሚቀጥሉት የአዲስ አመትና የመስቀል በአላት ሀገር ቤት ላለ ወዳጅ ዘመድ የሚልከውን ዶላርና ሌሎች የውጭ ምንዛሬዎችን በህጋዊ መንገድ በባንክ ቢልክ ሀገር የማዳን ተልእኮውን በበኩሉ እንደተወጣ ይቆጠራል፡፡ በትይዩ ገበያ የሚገኘው የተወሰነ የብር ጭማሪ ከሀገር አይበልጥምና በሀገር ቤት ያለነውም ዜጎች ዲያስፖራ ዘመዶቻችን ዶላሩን በባንክ እንዲልኩልን በማበረታት ለሀገራችን ኢኮኖሚ ጠቃሜታ እንዲውል ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡