ዘላቂ የሀይል ምንጭ ለኢኮኖሚ ልማት

July 9, 2021

በቅድሚያ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከጸጥታ ጉዳይነቱ ይልቅ የልማት ጉዳይ መሆኑን በማጤን በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስና የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት አቅጣጫ በአፍሪካ ህብረት ድርድር እንዲካሄድበት በመወሰኑ የተሰማንን ደስታ በገንዘብ ሚኒስቴር ስም እንገልጻለን፡፡

የኢትዮጵያ የአስር አመት መሪ የልማት እቅድ አላማ በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የጋራ ብልጽግናን እውን ማድረግ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ልማትና እድገት ተጨማሪ የሀይል ምንጭ እንደሚጠይቅ እሙን ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በግብርና፣ በኢንዱስትሪውና በአገልግሎቱ ዘርፍ እንዲሁም ቤት ውስጥ ፍጆታ ያለውን የሀይል እጥረት ማሟላትንም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ተጨማሪ የሀይል ፍጆታ የማሟላቱ ጉዳይ ፍትሀዊ የሐይል ተደራሽነትን ማረጋገጥንም ይጠይቃል፡፡

ኢትዮጵያ በገጸ ምድር የውሀ ሀብቷ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ስትሆን ከስምንቱ የወንዞቿ ተፋሰሶች 45 ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅም አላት፡፡ መንግስት የሀገሪቱን የሀይል እጥረት ለማስወገድ በዋና ዋናዎቹ የወንዞች ተፋሰሶች የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን በማልማት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም 6ሺ ሜጋ ዋት የሚያመነጨውንና ሲጠናቀቅም ከአፍሪካ ግዙፉ የሚሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብን እንዲሁም በቅርቡ የተጠናቀቀውንና 1ሺ 870 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን የጊቤ ሶስት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን ያካትታል፡፡

በአስር አመቱ መሪ የልማት እቅድ መሰረት በ2022 ዓ.ም የሀገሪቱ የሀይል ፍላጎት በ17ሺ ሜጋ ዋት እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በመንግስት ከሚለሙት የሀይል ምንጮች በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ ሀይል ተመርቶ የሀይል አቅርቦቱ እንዲሻሻልና ዘላቂ እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በ2009 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክት በአዋጅ ቁጥር 1076/2018 ተመስርቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት 23 የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክቶች የተለዩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ስምንት የጸሀይ አይል፣ አምስት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ፣ አምስት የንፋስ ሀይል፣ ሶስት የመንገድ፣ አንድ የቤቶችና አንድ የነዳጅ ዲፖ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዘጠኝ የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን ከነዚህ ወስጥ ሰባቱ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ከግሉ ዘርፍ የተወከሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ባላት ጂዮግራፊያዊ አቀማመጥ ከጸሀይ ሀይል ለማመንጨት እምቅ አቅም ያላት ሀገር ነች፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ስምንቱ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች 798 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ያመነጫሉ፡፡ በታህሳስ 2010 ዓ.ም የመጀመሪያውን የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የጸሀይ ሀይል ፕሮጀክት ጨረታን አለም አቀፉ የሀይል አመንጪና ውሀ አጣሪ ድርጅት ያሸነፈ ሲሆን አንድ ኪሎ ዋት የኤሉክትሪክ ሀይል በ2.526 የአሜሪካ ሳንቲም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ለመሸጥ የ20 አመታት ውል ተፈራርሟል፡፡

ኢትዮጵያ ከሀይድሮ ኤሌክትሪክ በተጨማሪ ታዳሽ ሀይሏን ከጂኦተርማልና ከንፋስ ሀይል ለማግኘት እየተጋች ሲሆን እ.ኤ.አ በ2018/19 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ ከጂኦተርማል 10ሺ ሜጋ ዋት ከንፋስ ሀይል ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት እምቅ ሀቅም አላት፡፡

የኢትዮጵያን የንፋስ ሀይል የተመለከትን እንደሆነ 34 ተርባኖች ያሉትና 51 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው አዳማ አንድ የንፋስ ሀይል ማመንጫ በሀገሪቱ የመጀመሪያው የሀንፋስ ሀይል ማመንጫ ሲሆን 153 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው አዳማ ሁለት ደግሞ በግዝፈቱ ከኬንው ሌክ ቱርካና በመቀጠል በአፍሪካ ሁለተኛው የንፋስ ሀይል ማመንጫ ነው፡፡

የጂኦተርማል ሀይልን በተመለከተም በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክት ኮርቤቲ ከሚባል የግል አልሚ ጋር መንግስት የተዋዋለ ሲሆን ድርጅቱ የሚያመርተውን 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ለማቅረብም ተፈራርሟል፡፡ በተጨማሪም መንግስት የጂኦተርማል ሀይል ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዘርፉ ለተሰማሩ የግል አልሚዎች የተለያዩ ድጋፎችንም በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽእኖና ውስጣዊ ያለመረጋገቶችን እየተቋቋመች ልማቷን ለቅጽበት ባለመዘንጋቷ ይኧው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ሙሌት ተጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ በብሩህ ተስፋ ተሞልቶ የሀገሪቱን ንጋት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ነው መንግስት ለልማትና እድገት ወሳኝ በሆነውን የኤሌክትሪክ ሀይል ልማት ላይ ተግቶ በመስራት ላይ የሚገኘው፡፡

በመጨረሻም የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የአባይን ውሃ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ተወያይተው የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ መወሰኑ የውሀና መስኖ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በምክር ቤቱ እንደ ገለጹት ግድቡን በደማችን፣ በላባችንና በእንባችን ለምንገነባው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ታላቅ ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምን ጊዜም በሀቅ ታሸንፋለች!!

 

471 Views