ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚያዊ ትብብር
Oct. 28, 2021
ኢትዮጵያ ብሄራዊ የልማት እቅድ ነድፋ እድገትና ልማቷን ለማፋጠን ከምታደርገው ጥረት በተጓዳኝ ከጎረቤቶቿ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር የምታደርገው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ ትናንት ጥቅምት 17 2014 ዓ.ም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የፋይናንስ ሚኒሰትሮች በበይነ ምረብ መክረዋል፡፡ የፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ምክክር በየሶስት ወራት የሚካሄድ ሲሆን የትናንቱ ምክክር ለዘጠነኛ ጊዜ የተካሄደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ከሆኑት ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኬኒያ ጋር የጎለበተ የኢኮኖሚ ትብብር ያስፈልጋታል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ አጽንኦት ሰጥተው እንደገለጹት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በትራንስፖርት፣ በንግድ፣ በገጠር ፋይናስ፣ በመጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠርና የበረሀ እንበጣን በመከላከል ረገድ ተባብረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ማእከላዊ ስፍራ የምትገኝ በመሆኗና ከሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር የምትዋሰን በመሆኗ ለኢኮኖሚያዊ ትብብሩ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እድገትና ልማትን እውን በሚያደርጉ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ማለተትም በመንገድ ትራንስፖርት ትስስር፣ በታዳሽ ሀይል ንግድ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ትስስር፣ በአርብቶ አደሮች ልማትና በአረንጓዴ ልማት ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ይኖራታል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ውስጣዊ ያለመረጋገት በህግ ማስከበሩ ሂደት ተወጥታ ፊቷን ወደ እድገትና ልማት በመመለስ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ውጤታማ ኢኮኖሚያዊ ትብብር የምትጫወተውን ሚና አጠናክራ የምትቀጥል ሲሆን ለተግባራዊነቱም የመንግስት አካላት፣ የዜጎች፣ የግሉ ዘርፍና የልማት አጋሮች ትብብርና ቅንጅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡